የካውንስሉ የአማራ ፖለቲካዊ ጉዳይ አስተባባሪ የስራ ክፍል መግቢያ
በአሁን ወቅት የአማራ ሁሉ ቅድሚያ እሳቤና ትኩረት የህልውና ትግል መዳረሻ ጥያቄ ነው። በዚህ የአማራ ትግል የዘር ፍጅት፣ የቅርስና የባህል መጥፋት፣ የቋንቋ መታፈን፣ የኢኮኖሚ ፍትህ ፣ የፓለቲካ ስልጣን ውክልና ፣ የታሪክ መዛባት ጥያቄዎች አሉት። እነዚህን ጥያቄዎች በሐቀኝነት ንኡስ ማህበረሰባዊ መርሆቹ ተመዝኖ መተንተን አለበት። አያሌ መስዋዕትነትን ከሚያስከፍል ድል ማግስት ብዙ የተለያዩ አላማና ዕርዮተ ዓለም ያላቸው ቡድኖች እና አደረጃጀቶች ለስልጣን ወደ ፊት ይመጣሉ። ነገር ግን ከፓለቲካ ቅድመ ዝግጅት ዕጦት የተነሳ በተጋድሎ የተገኘን ድል ተመልሶ እንዳይቀለበስ ቀደም ብለን በብልሃትና በሩቅ አስተዋይነት ላይ የተመሰረተ ርዕዮተ ዓለም መቅረፅ ይኖርብናል። በበርካቶች እንደሚገመተው ከዚህ በኋላ ሊመጣ የሚችለው የስርዓት ለውጥ አቅጣጫ በሶስት ይከፈላል።
1ኛ/ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የምታኖር በዜግነት ፓለቲካ የምትመራ ኢትዮጲያ።
2ኛ/ ያለው ስርዓት የዘር ፓለቲካው ተሻሽሎና ከአማራዉ የተወሰዱበትን መሬቶች በማስመለስ፣ ከክልል ውጭ ያሉት አማራወች በፌዴራል እና በክልል በቂ የህልዉና ዋስትና አግኝተዉ ይቀጥል የሚል።
3ኛ/ የአማራን ጥያቄና የሌሎች ኢትዮጲያን ወደድ ነገዶች የህልውና ጥያቄ አጣምሮ የሚመልስ አዲስ የፌድራል ስርአተ መንግስት እንዲመሰርት የሚሉ ናቸዉ።
እነዚህን እና ሌሎችንም ሊመጡ የሚችሉ ልዩነቶችን ቀድመን ካልተወያየንበት እና መፍትሔ ካልስቀመጥን የሽግግር ጊዜውን ፈታኝ ያደርጉታል። በአማራው ጥያቄዎች ላይ የማያቅማማ፣ ቀይ መስመሮችን በጥበብና ስልት የሚመራ የጀግና ፋኖ ታጋድሎ እንቅስቃሴን በውስጥና በውጭ ያለውን የዐማራ ህብረተሰብ ሰፊ የፖለቲካ ትስስርን ለመፍጠር አመቺ በሆነ መድረክ በተከታታይነት የመሰባስብና በጋራ መምከር፣ መወያየት እና ወደ ተግባር በመቀየር የጋራ የፖለቲካ እሳቤንና ግብ ማበጀት ይጠበቅብናል።
በሽግግሩ ወቅት ለሚደረጉ ውይይቶች እና ምክክሮች ቀይ መስመሮቻችንን ቀድሞ ማወቅ እና ማስቀመጥ መነሻ እና መዳረሻ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። መታቀፍ እና መታለፍ የሌለባቸው መስመሮች በግልጽ በማስቀመጥ ለደጋፊና ተከታይ ማህበረሰባችን የፖለቲካ መርህ ምዕዘን ማስቀመጥ እንችላለን ማለት ነው። በዚህም መሰረት የአማራን ዘር ፍጅት ከፈፀሙ እና የሐገር ነባር ሉዓላዊነትና፣ ሰንደቅዓላማ፣ ከማያምኑ እንድሁም የዘር ፓለቲካ፣ የሐይማኖት አለመረጋጋት ከሚፈልጉ ቡድኖች ጋር አንድነት ሊኖረን አይችልም ብለን የማንደራደርበት ጉዳይ ሊኖረን ይገባል። ስለዚህም የአማራ ጉዳይ ያገባኛል የሚል አካል በሙሉ ተሰባስቦ ልናያት የምንፈልገውን ኢትዮጵያ በቅድሚያ በቀለም እና በብራና በመቅረፅ የጋራ ራዕያችንን ማስቀመጥ ይኖርብናል።
በተለያዪ አካባቢዎች ያሉ ትዉልደ አማራወች ተሰባስበን በመወያየት የፖለቲካ ፖሊስ ሰነድ ግባአት ማዘጋጀት ያስፈልገናል።
በአማራው የህልውና ፖለቲካ ጉዳዮች ዙርያ የሚነሱ ነጥቦች ለይቶ ለውይይት በማቅረብ በአደባባይ ጉባኤ የፖለቲካ ውክልናን የሚያገኙ የአማራ ተጠሪዎች የሚቀርቡ መሰረተ ሃሳቦች ይሆናሉ። የፖለቲካ ፓርቲን ለሚያደራጁና ህዝብን ለማስተዳደር የሚቀርቡ የአማራ ወገኖች በዚህ ሂደት ቅድመ ፖለቲካ ፓርቲ ውይይቶች ምክረ ሃሳቦች ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በፖለቲካ ጉዳዮች ዙርያ በርካታ ርዕሶች መመልከት ይቻላል። ከነዚህም በጥቂቱ የህልውና ጥያቄ፣ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፣ የዘር ፍጅትና ካሳ፣ የባህል ወረራ፣ የራስ ገዝ ስልጣን መሰረቶች፣ የኢኮኖሚ ፍትህ፣ የፓለቲካ ውክልና፣ የአፅመ ዕርስት ነጠቃና መፈናቀል፣ የፀረ አማራ ትርክት መስተካከል የአማራ ተወላጅ ህጻናት በሚኖሩበት አካባቢ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የመነፈግ እና የእኩልነት ጥያቄዎች ናቸው።